መሠረታዊ ኦርቶዶክስ አስተምህሮ

 

የቅዱስ ጳውሎስ አስተምህሮዎች ምርጫ
1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ

ምዕራፍ 3: የጵጵስና ሹመት ሥርዓት

1 ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው። 
2 እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ የማይነቀፍ፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሰራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥ 
3 የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥ 
4 ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፤ 
5 ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል? 
6 በትዕቢት ተነፍቶ በዲያቢሎስ ፍርድ እንዳይወድቅ፥ አዲስ ክርስቲያን አይሁን። 
7 በዲያቢሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል። 
8 እንዲሁም ዲያቆናት ጭምቶች፥ በሁለት ቃል የማይናገሩ፥ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይጎመጁ፥ 
9 ነውረኛ ረብ የማይወዱ፥ በንጹሕ ሕሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል። 
10 እነዚህም ደግሞ አስቀድሞ ይፈተኑ፥ ከዚያም በኋላ ያለ ነቀፋ ቢሆኑ በዲቁና ሥራ ያገልግሉ። 
11 እንዲሁም ሴቶች ጭምቶች፥ የማያሙ፥ ልከኞች፥ በነገር ሁሉ የታመኑ ሊሆኑ ይገባቸዋል። 
12 ዲያቆናት ልጆቻቸውንና የራሳቸውን ቤቶች በመልካም እየገዙ እያንዳንዳቸው የአንዲት ሴት ባሎች ይሁኑ። 
13 በዲቁና ሥራ በመልካም ያገለገሉ ለራሳቸው ትልቅ ማዕርግና በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው እምነት ብዙ ድፍረት ያገኛሉ። 
14 ፈጥኜ ወደ አንተ እንድመጣ ተስፋ አድርጌ ይህን እጽፍልሃለሁ። 
15 ብዘገይ ግን፥ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው። 
16 እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ።

 

ምዕራፍ 4: ስለ ሐሰተኞች የተነገረ ትንቢት
1- 2 መንፈስ ግን በግልጥ። በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል፤ በገዛ ሕሊናቸው እንደሚቃጠሉ ደንዝዘው፥ 
3 እነዚህ ውሸተኞች መጋባትን ይከለክላሉ፥ አምነውም እውነትን የሚያውቁ ከምስጋና ጋር ይቀበሉ ዘንድ እግዚአብሔር ከፈጠረው መብል እንዲርቁ ያዝዛሉ። 
4 እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነውና፥ ከምስጋናም ጋር ቢቀበሉት የሚጣል ምንም የለም፤ 
5 በእግዚአብሔር ቃልና በጸሎት የተቀደሰ ነውና።


ምዕራፍ 5: ሽማግሌዎችን ስለ ማክበር እና መበለቶችን ስለ መርዳት

1- 2 ሽማግሌ የሆነውን አትገሥጸው፥ እርሱን ግን እንደ አባት፥ ጎበዞችን እንደ ወንድሞች፥ የሸመገሉትን ሴቶች እንደ እናቶች፥ ቆነጃጅቱን እንደ እኅቶች በፍጹም ንጽሕና ለምናቸው። 
3 በእውነት ባልቴቶች የሆኑትን ባልቴቶች አክብር። 
4 ማንም ባልቴት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት፥ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተ ሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል ያሳዩ ዘንድ፥ ለወላጆቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ ነውና። 
5 ብቻዋንም ኖራ በእውነት ባልቴት የምትሆን በእግዚአብሔር ተስፋ ታደርጋለች፥ ሌትና ቀንም በልመና በጸሎትም ጸንታ ትኖራለች፤ 
6 ቅምጥሊቱ ግን በሕይወትዋ ሳለች የሞተች ናት። 
7 ያለ ነቀፋ እንዲሆኑ ይህን ደግሞ እዘዝ። 
8 ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው። 
9 ባልቴት በመዝገብ ብትጻፍ ዕድሜዋ ከስድሳ ዓመት እንዳያንስ፥ የአንድም ባል ሚስት የነበረች እንድትሆን ያስፈልጋል፤ 
10 ልጆችን በማሳደግ እንግዶችንም በመቀበል፥ የቅዱሳንንም እግሮች በማጠብ፥ የተጨነቁትንም በመርዳት በጎንም ሥራ ሁሉ በመከተል፥ ይህን መልካም ሥራ በማድረግ የተመሰከረላት ልትሆን ይገባል። 
11 ባል የሞተባቸውን ቆነጃጅት ግን አትቀበል፤ በክርስቶስ ላይ ተነሥተው ሲቀማጠሉ ሊያገቡ ይወዳሉና፤ 
12 የፊተኛውንም እምነታቸውን ስለ ናቁ ይፈረድባቸዋል፤ 
13 ከዚህም ጋር ቤት ለቤት እየዞሩ ሥራን መፍታት ደግሞ ይማራሉ፥ የማይገባውንም እየተናገሩ ለፍላፊዎችና በነገር ገቢዎች ይሆናሉ እንጂ፥ ሥራ ፈቶች ብቻ አይደሉም። 
14 እንግዲህ ቆነጃጅት ሊያገቡ፥ ልጆችንም ሊወልዱ፥ ቤቶቻቸውንም ሊያስተዳድሩ፥ ተቃዋሚውም የሚሳደብበትን አንድን ምክንያት ስንኳ እንዳይሰጡ እፈቅዳለሁ፤ 
15 ከአሁን በፊት አንዳንዶች ሰይጣንን እንዲከተሉ ፈቀቅ ብለዋልና። 
16 ባልቴቶች ያሉት የሚያምን ቢሆን ወይም የምታምን ብትሆን፥ ይርዱአቸው፥ ቤተ ክርስቲያንም እውነተኞችን ባልቴቶች እንድትረዳ አይክበዱባት። 

 

ምዕራፍ 6: ከክህደትና ገንዘብን ከመውደድ ስለ መራቅ
6 ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ 
7 ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ 
8 አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 
9 ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። 
10 ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። 
11 አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል። 
12 መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ። 
13 ሁሉን በሕይወት በሚጠብቅ በእግዚአብሔር ፊት፥ በጴንጤናዊውም በጲላጦስ ዘንድ መልካሙን መታመን በመሰከረ በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት አዝሃለሁ፤ 
14 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ ያለ እድፍና ያለ ነቀፋ ሆነህ ትእዛዙን ጠብቅ፤ 
15 ያንም መገለጡን በራሱ ጊዜ ብፁዕና ብቻውን የሆነ ገዥ፥ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ፥ ያሳያል። 
16 እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኃይል ይሁን፤ አሜን። 
17 በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፥ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው። 
18-19 እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፥ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፥ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው። 
20 ጢሞቴዎስ ሆይ፥ በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ፥ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ፤ 
21 ይህ እውቀት አለን ብለው፥ አንዳንዶች ስለ እምነት ስተዋልና። ጸጋ ከአንተ ጋር ይሁን።