ምዕራፍ 2: ስለ ክርስቲያን ኑሮ ሥርዐት 1 አንተ ግን ሕይወት ለሚገኝበት ትምህርት የሚገባውን ተናገር። 2 ሽማግሌዎች ልከኞች፥ ጭምቶች፥ ራሳቸውን የሚገዙ፥ በእምነትና በፍቅር በመጽናትም ጤናሞች እንዲሆኑ ምከራቸው፤ 3 እንዲሁም አሮጊቶች ሴቶች አካሄዳቸው ለቅዱስ አገልግሎት የሚገባ፥ የማያሙ፥ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይገዙ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ ይሁኑ፤ 4- 5 ቆነጃጅትም የእግዚአብሔር ቃል እንዳይሰደብ፥ ባሎቻቸውን የሚወዱ፥ ልጆቻቸውን የሚወዱ፥ ራሳቸውን የሚገዙ፥ ንጹሖች፥ በቤት የሚሠሩ፥ በጎዎች፥ ለባሎቻቸው የሚታዘዙ እንዲሆኑ ይምከሩአቸው። 6 ጎበዞችም እንዲሁ ራሳቸውን እንዲገዙ ምከራቸው። 7- 8 የሚቃወም ሰው ስለ እኛ የሚናገረውን መጥፎ ነገር ሲያጣ እንዲያፍር፥ በነገር ሁሉ መልካምን በማድረግህ ምሳሌ የሚሆን ራስህን አሳይ፤ በትምህርትህም ደኅንነትን፥ ጭምትነትን፥ ጤናማና የማይነቀፍ ንግግርን ግለጥ። 9- 10 ባሪያዎች ስለ መድኃኒታችን ስለ እግዚአብሔር የሚሆነውን ትምህርት በሁሉ ነገር ያስመሰግኑ ዘንድ፥ ለገዛ ጌቶቻቸው እንዲገዙ በሁሉም ደስ እንዲያሰኙ፥ ሳይቃወሙና ሳይሰርቁም በጎ ታማኝነትን ሁሉ እንዲያሳዩ ምከራቸው። 11 ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ 12-13 ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤ 14 መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል። 15 ይህን በሙሉ ሥልጣን ተናገርና ምከር ገሥጽም፤ ማንም አይናቅህ።
1- 2 ለገዦችና ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ፥ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ፥ ማንንም የማይሰድቡ፥ የማይከራከሩ፥ ገሮች፥ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ ኣሳስባቸው። 3 እኛ ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና፤ የማንታዘዝ፥ የምንስት፥ ለምኞትና ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ፥ በክፋትና በምቀኝነት የምንኖር፥ የምንጣላ፥ እርስ በርሳችን የምንጠላላ ነበርን። 4 ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥ 5 እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤ 6- 7 ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው። 8 ቃሉ የታመነ ነው። እግዚአብሔርንም የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲጸኑ፥ እነዚህን አስረግጠህ እንድትናገር እፈቅዳለሁ። ይህ መልካምና ለሰዎች የሚጠቅም ነው፤ 9 ነገር ግን ሞኝነት ካለው ምርመራና ከትውልዶች ታሪክ ከክርክርም ስለ ሕግም ከሚሆን ጠብ ራቅ፤ የማይጠቅሙና ከንቱዎች ናቸውና፤ 10-11 መለያየትን የሚያነሣ ሰው ጠማማ እንዲሆን በራሱም ላይ ፈርዶ ኃጢአትን እንዲያደርግ አውቀህ፥ አንድ ጊዜ ሁለት ጊዜም ከገሠጽኸው በኋላ እንዲህ ከሚመስል ሰው ራቅ።
|