የቅዱሳን ሕይወት

 

ቅድስት ማክሪና

በከፊል ከሚከተለው ድረገጽ የተወሰደ፡ https://www.pemptousia.gr/2014/07/agia-makrina/

 በሜትሮፖሊታን ዳዮኒሲዮስ ዘኮዛኒ

‹‹ቅዱሳት ሥዕላት›› - አፖስቶሊክዲያኮኒያ ኅትመት

 


በታሪክ መዛግብት ሆነ የቤተክርስቲያኒቷ ታሪክ የታላላቅ ወንዶችን ብቻ ሳይሆን የታላላቅ ሴቶችንም ታሪክ መዝግቦ አቆይቶልናል፡፡ በዚህም ምክንያት ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ገላቲያ ምዕመናን የላከው መልእክት ውስጥ የሚገኘው ‹‹ወንድም ሴትም የለም…›› [ገላ 3፡28] የሚለውን ቃል በዚህ ቦታ መጥቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህም የሚጠቁመው በክርስቶስ ኅብረት ውስጥ ‹ወንድ› እና ‹ሴት› የሚል መለያ አለመኖሩን ነው፡፡ ሁለቱም ጾታዎች እኩል ዋጋ ያለቸው፣ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ እና የተከበሩም ናቸው፡፡

ቅድስት ማክሪና

በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ስሟ እና ገድሏ በደንብ ከታወቁ እና ከፍተኛ አክብሮት ከሚቸራቸው ሴቶች መካከል ቅድስት ማክሪና ተጠቃሽ ናት፡፡

ቅድስት ማክሪና የታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ እኅት ስትሆን፤ ለቤተክርስቲያን ሦስት ጳጳሳትን ካበረከተና ዘጠኝ ልጆች ካሉበት ቤተሰብ መካከልም የመጀመሪያ ልጅ ናት፡፡ የትውልድ ስፍራዋም የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ግዛት፣ ሰፊ የሆነ ቤተክርስቲያናዊ ትውፊት ባለቤት እና የብዙ ቅዱሳን አልፎም የቤተክርስቲያን መሪዎች መገኛ የሆነው ቀጰዶቂያ ነው፡፡ የእርሷ ቤተሰቦችም በቀጰዶቂያ እጅግ የታወቁ፤ ቀደምት አያቶቻቸውም በቤተክርስቲያን የሰማዕትነት ዘመን ሰማዕታት ሆነው ያለፉ እና ከገባሬ ተዓምራት ቅዱስ ጎርጎሬዎስ ሥር የተማሩ ናቸው፡፡

የኑሲስ ከተማ ጳጳስ የነበረው ወንድሟ ቅዱስ ጎርጎሬዎስ የሕይወቷን ገድል መዝግቦ ቢያቆይልንም፤ ሌላኛው ወንድሟ ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ደግሞ ስለ ሕይወቷ ብዙ ነገሮችን አንድናውቅ የሚያስችሉ መረጃዎችን ሰጥቶናል፡፡ ቅዱስ ጎርጎሬዎስ ዘኑሲስ የእኅቱን ታሪክ መመዝገብ ሲጀምር እንዲህ በማለት ነው፡ ‹‹የምጽፋቸው ነገሮች ከንባብ ሳይሆን ከሕይወት ልምድ ያገኘኋቸው በመሆናቸው ተዓማኒነት ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህን ነገሮች በዝርዝር እነግራችኋለሁ፤ የሌሎችን ምስክርነትንም አልጠቅስም፡፡››

ማክሪና ለቤተሰቦቿ የመጀመሪያ ልጅ ስትሆን ቤተሰቦቿም በትጋት አሳድገዋታል፡ ‹‹… በዜማ ተደርገው የሚዜሙ ጽሑፎችንም ጭምር ታውቅ ነበር፡፡›› እንዲል፡፡ ይህም ማለት ከሌላው ነገር በተጨማሪ መዝሙረ ዳዊትን በአጠቃላይ በቃሏ ታውቀው ነበር፡፡


ገና በልጅነቷ ወላጅ አባቷ ለአንድ ጥሩ ወጣት ቢያጫትም፤ የትዳራቸው ቀን ሳይደርስ በፊት
ወጣቱ በሞት ተለየ፡፡

ይህም ለማክሪና በቂ ነበር፡፡ ትዳሩ እንደተፈጸመ እና እንዳገባች ራሷን በመቁጠር፤ ለአባቷ ዐሳብ ታማኝ ሆና ቀጠለች፤ ወንድሞቿንም በማሳደግ ሒደት እናቷን በማገዝ ላይ አተኮረች፡፡ በቤት ውስጥም ወንድሞቿ እጅግ ያከብሯት እና እንደ ሁለተኛ እናት ያዩዋት ነበር፡፡ቅዱስ ባስልዮስ የነበረበትን የሕግ ሙያ በመተው ወደ ምንኩስና ሕይወት እንዲገባ ያሳመነችውም እርሷ ነበረች፡፡ አባቷ ከሞተ በኋላም ዘጠነኛ ወንድሟ የነበረውን ጴጥሮስን ማሳደግና በትምህርቱም መርዳት ጀመረች፤ ‹‹እጅግ ከፍተኛ ወደሆነ የእውቀት ደረጃ መራችው›› እንዲል፡፡ ይህ ወንድሟ በኋላ ላይ የሰቫስቲያ ሊቀ-ጳጳስ ሊሆን ችሏል፡፡


ሆኖም ግን ቅድስት ማክሪና ‹‹የሕይወት መምህር›› እና ‹‹ሁለተኛ እናት›› ብቻ አልነበረችም፤ ቅድስት የሆነች መነኩሴም ጭምር እንጂ፡፡ ሁሉም ወንድሞቿ ለአቅመ አዳም ደርሰው የራሳቸውን መንገድ ከያዙም በኋላ፤ በፖንተስ ከተማ ወደሚገኘው የቤተሰቦቿ ቤት በመሄድ ትልቅ የሴቶች ገዳምን መሠረተች፡፡ ቅዱስ ጎርጎሬዎስ ዘኑሲስም ‹የመልካም ምግባራት መማሪያ ቦታ› በማለት ስለሚጠራው ይህ ገዳም ሲናገር፡ ‹‹በመንፈሳዊ እናትነት የወለደቻቸው እና በትኩረትና ትጋትም ወደ ፍጹምነት ደረጃ ያደረሰቻቸው በዙሪያዋ የሚገኙት ደናግላን ብዙ ነበሩ፡፡ የመላእክትን ኑሮ በሰው ልጅ ሰውነት ኖራዋለች…›› እንዲል፡፡ ዘለዓለማዊ ሕይወት ለማግኘት የራሳቸውን ሕይወት የተዉ ቅዱሳን ሴቶች….

የተወደደች ማክሪና ወንድሟ ቅዱስ ጎርጎሬዎስ በሞት ከተለየ ከአንድ ዓመት በኋላ፣ ማለትም በ380 ዓ.ም፣ ተጋድሎዋን ጨርሳ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች፡፡ በሞተች ጊዜ ከአጠገቧ የነበረው፣ የተገለጡ የአይኖቿን ሽፋሽፍትም የከደነው ቅዱስ ጎርጎሬዎስ፤ የመጨረሻ ደቂቃዎቿን ስሜት በሚነካ ሁኔታ ይገልጸዋል፡፡ በሞት ከመለየቷም ቀደም ብሎ የጸለየችውን በእምነትና ተስፋ የተሞላ ጸሎት መዝግቦልናል፤ አንዲህም ይላል፡ ‹‹ጌታ ሆይ፣ አንተ ከሞት ፍርሃት ነጻ አወጣኸን፡፡ የዚህን ሕይወት መጨረሻም የእውነተኛ ሕይወት መጀመሪያ አደረግክልን፡፡›› ትንሣኤንም ተስፋ አድርጋ፣ ቅድስት ማክሪና ‹‹ከሞት ወደ ሕይወት›› ተሸጋገረች፡፡

ድምጽዋን ዝቅ አድርጋ ራሷን በትእምርተ መስቀል እያማተበች ትጸልይ ነበር፡ ‹‹የመስቀሉን ምልክትም በዓይኗ፣ በአፏና በልቧ ላይ ታደርግ ነበር፡፡›› እንዲል፡፡
አሜን፡፡






                                                                ዝግጅት በ: ሮ. ኢ.፣ ፍ. አ.