ትዳርና የቤተሰብ ኑሮ

 

ለኦርቶዶክስ ጋብቻ መመሪያ

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሰባት ስብከቶች ስለ ወንድ እና ሴት፡የትዳር ሕይወትና የትዳር ላይ ጥቃት)

1.  መግቢያ


አንዲት፣ ቅድስት፣ ኵላዊት እና ሐዋርያዊት በሚሉ ቅጽሎች የምትጠራው ቅድስት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የታሪኳ ሥረ-መሠረት ሐዋርያት የበዓለ አምሳ ዕለት የተቀበሉት መለኮታዊ መገለጥ ነው፡፡ ይህም ኦርቶዶክሳዊ መገለጥ እስካሁን ድረስ ኦርቶዶክሳዊያን በሚገኙባቸው በመካከለኛው ምሥራቅ፣ ታናሽ እስያ፣ ሜዲትራንያን አውሮፓ፣ አፍሪቃ እና ሕንድ በሐዋርያት እና በተከታዮቻቸው አማካኝነት ሊሰራጭ ችሏል፡፡ በቀደሙት ዘመናት ውስጥ ክርስትና በሮም ይፋዊ የመንግሥት ሃይማኖት እስከሆነበት ወቅት ድረስ ክርስቲያኖች በሮማውያን ቄሳሮች ከፍተኛ በደል ይደርስባቸው ነበር፡፡ ምንም ስንኳ እነዚህ ቀደምት ክርስቲኖች በአጠቃላይ የአንዲት፣ ቅድስት፣ ኵላዊት እና ሐዋርያዊት የሆነችው ቤተክርስቲያን አካል የነበሩ ቢሆንም የተለያዩ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ እና ነገረ-መለኮታዊ ሁኔታዎች በምሥራቃውያን እና ምዕራባውያን ክርስቲያኖች መካከል መከፋፈልን አስከትለዋል፡፡

በወቅቱ የተከሰቱ የተለያዩ ፖለቲካዊ ኩነቶች የምዕራቧ ቤተክርስቲያን በአስተምህሮ እና ነገረ-መለኮታዊ ጉዳዮች ላይ ራሷን እንድትለይ [ተለይታ እንድትወጣ] አድርጓታል፡፡ ይህም ደግሞ በዐሥራ አንደኛው መቶ ክ/ዘመን በቤተክርስቲያን ውስጥ ለተፈጠረው ክፍፍል ምክንያት ሆኗል
[1]፡፡ ምሥራቃውያን የቤተክርስቲያን አባቶች [ኦርቶዶክሳዊያን አባቶች] አዳዲስ አስተምህሮዎችን ሳይጨምሩ፤ ነገር ግን በግሪክ ቋንቋ የተጻፉ ጥንታዊ መዛግብቶች ላይ በመመርኮዝ እና የጥንታዊቷን ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን የነገረ-ድኅነት መልእክት በሚገልጽ መልኩ ነገረ መለኮታዊ አስተምህሮውን ለመረዳት የሚያስችለውን ፍልስፍናዊ መዋቅር አስተካክለዋል፡፡ በጥንታዊቷ ቤተክርስቲያን አረዳድ መሠረት የእነርሱ ሥራ ምድራዊ የአእምሮ ፈጠራ እና የሥነ-አመክንዮ ፍልስፍና ውጤት ሳይሆን ከምናኔ[2] እና አብርሆት [ከመንፈስ ቅዱስ በሆነ መገለጥ] የመነጨ ነገረ-መለኮታዊ አስተምህሮ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ [በግሪኩ ‹ክሪሶስቶሞስ› ተብሎ ይጠራል፤ ትርጉሙም አፈ-ወርቅ ማለት ነው] ከእነዚህ ኦርቶዶክሳዊ አባቶች መካከል እጅግ የታወቀ የነገረ-መለኮት ሊቅ እና ቅዱስ አባት ነው፡፡[3]  

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የተወለደው የሮም ርዕሰ ከተማ በነበረችው በአንጾኪያ ሲሆን ጊዜውም በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ነው፡፡ በወቅቱ ዝነኛ ከነበረው የንግግር ጥበብ መምህር ሊባኒዮስ ሥር ፍልስፍናን ቢያጠናም በመጨረሻ ግን ወደ ኦርቶዶክሳዊነት በመመለስ ለተወሰነ ጊዜ የምናኔ ሕይወት ኖሯል፡፡ በቅስና ማዕርግ በአንጾኪያ ካቴድራል ሲያገለግል ከቆየ በኋላ የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ መሆን ችሏል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ብዙ ስብከቶችን የሰበከ ሲሆን፤ በእነዚህም ስብከቶቹ ውስጥ የሐዋርያቱን ትምህርት፤ በተለይም ደግሞ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ክርስትና ለመጡ የመጀመሪያ መቶ ክፍለዘመን ምዕመናን የጻፋቸውን መልእክታት በሚገባ አብራርቶ ተርጉሟል፡፡
[4] ትርጓሜዎቹም በአንጾኪያ ከተማ[5] ውስጥ በመንሰራፋት ላይ የነበረውን ዓለማዊነት እና ሴሰኝነት በመዋጋት የምዕመናኑንም መንፈሳዊ ሕይወት በሐዋርያዊ ትምህርት ለማሻሻል ያለሙ ነበሩ፡፡

ይህ ጥናታዊ ጽሑፍ ከቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሰባት ስብከቶች የተውጣጣ ሲሆን፤ በወንድ እና ሴት የጋብቻ ሕይወት ላይ ያጠነጥናል፡፡ ስብከቶቹንም በምልከታ እና ልምድ በዳበረ ኦርቶዶክሳዊ አስተሳሰብ (ፍሮኒማ)
[6] ለመመልከት ሙከራ ተደርጓል፡፡ ዓላማውም የቤተክርስቲያን አባቶች አስተምህሮን ለምዕመናን ነባራዊ ሁኔታዎች የበለጠ በማቅረብ ስለ ኦርቶዶክሳዊ እምነት ያላቸውን አረዳድ ከፍ ማድረግ ነው፡፡ የዚህ ጥናት ጸሐፊም የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርቶች ጠንካራ የሆነ ባህላዊ መሠረት ባላቸው የኦርቶዶክስ ማኅበረሰቦች ውስጥ ከሴቶች እና ትዳር ጋር ተያይዞ ያለውን መጥፎ ልማድ ለመቅረፍ ወሳኝ መሆኑን ታምናለች፡፡

ይህን መሰል ተግባራት ጠንካራ ባህላዊ መሠረት ባላቸው የኦርቶዶክስ ማኅበረሰቦች ውስጥ የተለመዱ ሲሆኑ፤ የኦርቶዶክስ ነገረ-መለኮታዊ አስተምህሮዎችን በአግባቡ ካለመረዳት እና በእምነቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸውን ተግባራት በተመለከተ ወደ ባህላዊ እና ማኅበረሰባዊ እይታዎች ከማዘንበል ሊመነጭም ይችላል፡፡ በተጨማሪም እነዚህ አስተሳሰቦች በቤተክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ በሚገኙ ካህናት እና አገልጋዮች መካከል ተገቢውን የትርጓሜ ዘይቤ ባልተከተለ መልኩ ስለ ወንድ እና ሴት የጋብቻ ጥምር ግንኙነት በሚደረግ ውይይት ወይም ትምህርት በሕዝቡ ዘንድ ጠንካራ ቦታ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ለአብነት ያህል ቤተሰብን ከመበታተን በማዳን ወይንም ከባድ በሆኑ ሁኔታዎች ጊዜ ይቅርታን ተመራጭ በማድረግ ላይ ያተኮረ ትምህርት በባሎቻቸው ጥቃት የሚደርስባቸው ሚስቶች ሁኔታዎችን በዝምታ እንዲያልፉ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማም በወንድ እና ሴት የጋብቻ ጥምር ግንኙነት ዙሪያ በኦርቶዶክስ ምዕመናን እና ካህናት ዘንድ ሊኖሩ የሚችሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን መቅረፍ እና በጉዳዩ ዙሪያ ያሉ መልካም ያልሆኑ ባህላዊ እና ማኅበረሰባዊ አስተሳሰቦችን መቀልበስ ነው፡፡


[1] ቀሲስ ጆን ሮማኒዴስ እንደገለጹት ከሆነ ይህ ክፍፍል የተከሰተው በምዕራብ እና ምሥራቅ ክርስቲያኖች መካከል ሳይሆን ይልቁንም በምሥራቅ ሮማኒያ እና ለፖለቲካ ጥቅማቸው ሲሉ የቀደምት ቤተክርስቲያኗን አስተምህሮ የበረዙት የሮማ ግዛት ገዢዎች መካከል ነው፡፡ ይህንን ምንጭ ይመልከቱ፡- John Romanides, Romiosini, Romania, Roumeli (Thessaloniki: Pournaras, 1975)

 

[2] ἄσκησις’; ወደ አማርኛ ቋንቋ ሲመለስ ‹ገቢር፣ ልምድ፣ ተግባር፣ ልምምድ› የሚል ትርጉም ይኖረዋል፡፡

 

[3] የግሪኩ ስንክሳር እንደሚገልጸው ከሆነ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ 804 ድርሳኖች ከመጥፋት ተርፈዋል፡፡ ይህንን ምንጭ ይመልከቱ፡- Ορθόδοξος Συναξαριστής, “Άγιος Ιωάννης ο Χρυσόστομος Αρχιεπίσκοπος Κωνσταντινούπολης,”http://www.saint.gr/3021/saint.aspx

 

[4] የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በቅዱስ ጳውሎስ የተጻፉ አሥራ አራት መልእክታትን ትቀበላለች፡፡ እነዚህም፡- ሮሜ፣ አንደኛ/ሁለተኛ ቆሮንጦስ፣ ገላትያ፣ ኤፌሶን፣ ፊልጵስዩስ፣ ቆላስይስ፣ አንደኛ/ሁለተኛ ተሰሎንቄ፣ አንደኛ/ሁለተኛ ጢሞቲዎስ፣ ቲቶ፣ ፊልሞና እና ዕብራውያን ናቸው፡፡ ከኢነዚህ ውስጥ አሥራ ሦስቱ ስሙን ሲጠቅሱ አንዱ ግን (ዕብራውያን) ስሙን አይጠቅስም፡፡ ዘመናዊ ጥናት ከእነዚህ መልእክታት ውስጥ የተወሰኑት በጳውሎስ የመጻፋቸውን ነገር ይጠራጠራል፡፡ 

 

[5] ዘመናዊ ሊቃውንት የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የተለያዩ ተግሳጾች በየት ቦታ እንደተነገሩ አይስማሙም፡፡ ሆኖም ግን ብዙዎቹ ተግሳጾቹ በአንጾክያ ከተማ የተነገሩ መሆናቸው ላይ በብዛት ስምምነት አለ፡፡

 

[6] φρόνημα የሚለው ቃል ‹ንቃተ ሕሊና› የሚል ትርጉምን ሊይዝ ይችላል፡፡ የግሪኩ ቃል እንደሚገልጸው ከሆነ ፍሮኒማ ኦርቶዶክሳዊ እምነትን በተግባር ከመኖር የሚመነጭ እይታ ነው፡፡ እንዲህ የተባለበት ምክንያት በጥናቱ ውስጥ የሚገለጽ ይሆናል፡፡

  ወደ ይዘቶች ተመለስ ምዕራፍ 2