ትዳርና የቤተሰብ ኑሮ

 

ለኦርቶዶክስ ጋብቻ መመሪያ

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሰባት ስብከቶች ስለ ወንድ እና ሴት፡የትዳር ሕይወትና የትዳር ላይ ጥቃት)

2. የባህል መሸርሸር እና የእምነት መበረዝ


በታሪክ ውስጥ ስንመለከት የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስቀድመው በአንድ ቦታ ከነበሩ ማኅበረሰባዊ እና ፖለቲካዊ ሥርዓቶች ጋር ጥንቃቄ የተሞላበት ግንኙነት መሥርታ፤ በዚህም ውስጥ ኦርቶዶክሳዊነት ቀድመው ከነበሩት ሥርዓቶች ጋር ሲነጻጸር ያለውን ሁለንተናዊ ብልጫ እና በአዳዲስ አማኞችም ዘንድ እውነተኛውን የክርስትና መልእክት በተገቢው መንገድ ለማስረጽ ባለመ ሁኔታ ውስጥ ወንጌልን ለማሰራጨት ብዙ ሠርታለች፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎች እንዲያውም፤ የአካባቢው ቀደምት አካሄድ የክርስትና መልእክትን የማይጋፋ ሆኖ ከተገኘ ወይንም ደግሞ ቤተክርስቲያኒቷ ለአዳዲስ አማኒያን አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ላለመፍጠር ስትል ነባር ሥርዓቶችን አቅፎ የመጓዝ አካሄድን የተጠቀመችበት ሁኔታ አለ[1]፡፡ በዚህም ምክንያት አስቀድመው የነበሩ ማኅበረሰባዊ አወቃቀሮች በክርስትና ሳይዋጡ አብረው መጓዝ ችለዋል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች እና ማኅበረሰቦች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የቤተክርስቲያን አባቶች ነባር እሳቤዎቹን ይገነዘቧቸው የነበረ ሲሆን አላስፈላጊ የሆኑትንም በግልጽ ይኮንኑ ነበር፡፡ ለዚህም እንደ አብነት የሚጠቀሰው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ባርነትን የኮነነበት መንገድ ነው[2]፡፡ 

በሌላ በኩል ደግሞ በኦርቶዶክሳዊ ማኅበረሰቦች ውሰጥ ከዘመኑ ታሪክ ጋር ተያይዘው ያሉት ማኅበረሰባዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ኩነቶች፤ በወቅቱ ነገረ-መለኮታዊ ትምህርቶች በካህናት እና አገልጋዮች የሚታዩበትን መንገድ እና በካህናቱ በኩል ለምዕመኑ የሚደርሱበት ዘዴ ላይ ተጽእኖን ማሳደራቸው አይቀርም
[3]፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በገነነችባቸው አካባቢዎች ላይ የሚካሄዱ ውይይቶች እና ስብከቶች ከፖለቲካዊ፣ ማኅበረሰባዊ፣ ባህላዊ እና ሌሎችም የተለያዩ አቅጣጫዎች አንጻር እንዲቃኙ በመሆናቸው ለመበረዝ ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች፤ የኦርቶዶክስ አባቶች ምንም እንኳ በተለያየ ዘመን ቢኖሩም፤ ያንጸባርቁት ከነበረው እና ታሪካዊ መሠረት ካለው ኦርቶዶክሳዊ አስተሳሰብ (ፍሮኒማ) ተለየቶ ሊታይ ይገባዋል፡፡


[1] ይህ አካሄድ የሚታየው ቅዱስ ጳውሎስ ‹ለማይታወቅ አምላክ› በሚል የተጻፈውን የግሪክ ጽሑፍ መሠረት አድርጎ አቴናውያንን ለክርስትና ሲያስተዋውቅ ነው፡፡(ሐዋ 17፡23)

 

[2] እዚህ ጋር ነባቤ መለኮት ቅዱስ ጎርጎሬዎስን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እርሱም ለዘማዊ ሴት ቅጣት በማዘዝ ዘማዊ የሆነ ወንድን ግን ችላ የሚለውን ሕግ ተመልክቶ እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር፡- “Τι δήποτε γαρ το μεν θήλυ εκόλασαν, το δε άρρεν επέτρεψαν; Και γυνή μεν κακώς βουλευσαμένη περί κοίτην ανδρός μοιχάται και πικρά εντεύθεν τα των νόμων επιτίμια, ανήρ δε καταπορνεύων γυναικός ανεύθυνος; Ου δέχομαι ταύτην την νομοθεσίαν, ουκ επαινώ την συνήθειαν. Άνδρες ήσαν οι νομοθετούντες, διά τούτο κατά γυναικών η νομοθεσία.” ይህንን ስንተረጉመውም ‹‹ሴቷን የሚቀጧት ወንዱን ግን ይቅር የሚሉት ስለምንድር ነው; ሴቲቷ ዘማዊ በመሆን የመኝታን ክብር ስታረክስ በከባድ ቅጣት ትቀጣለች፡፡ ወንዱ ግን ከሌሎች ሴቶች ጋር ሲሄድ የማይቀጣው ስለምንድር ነው፡፡ ይህንን ሕግ አልቀበልም፤ እኮንነዋለሁም፡፡ ይህንን ሕግ የሰሩት ወንዶች ናቸው፤ ሕጉ ሴቶች ላይ የሚበረታውም ስለዚህ ነው፡፡›› የሚከተለውን ምንጭ ይመልከቱ፡- Patrologiae Graecae Tomus XXXVI: St. Gregorius Nazianzenus. ΛΟΓΟΣΛΖ’ (Migne, 1858).
[3] ለአብነት ያህል፡- ታሪካዊ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ምዕመናንን በተመለከተ ኤልሳቤጥ ጋዚን ስትጽፍ እንዲህ ትላለች - ‹‹እነዚህ ማኅበረሰቦች ኦርቶዶክስ ይባሉ እንጂ፣ የአካባቢው ዘመናዊ ታሪክ ቃኝተን ቤተክርስቲያን ልጆቿን በተገቢው መንገድ እንድታስተምር የማይፈቅዱ ኢስላማዊ እና ኮሚኒስት ኃይሎች እንደነበሩባት ስንረዳ፤ ከዚህ አንጻር እውነተኛው ኦርቶዶክሳዊ ኤቶስ-ባሕርይ ምን ያህል በእነዚህ ማኅበረሰቦች ውስጥ ሊገኝ እንደሚችል ጥያቄ ማንሳታችን አይቀርም፡፡›› የሚከተለውን ምንጭ ይመልከቱ፡- Elizabeth Gassin, “Eastern Orthodox Christianity and Mens Violence against Womenin Religion and Mens Violence against Women, A. Johnson, ed. (Springer: New York, 2015), 165.

 



ምዕራፍ 1 ወደ ይዘቶች ተመለስ ምዕራፍ 3